የእንቁጣጣሽ በዓል ሲከበር ለሚሊኒየሙ በዓል አከባበርም ዝግጅት እንዲደረግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ጳጉሜን 4/1998/ዋኢማ/ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱን የ1999 ዓ.ም. የእንቁጣጣሽ በዓል ሲያከብር ብቸኛ የጥቁር ህዝቦች በዓል የሆነውና በ2000 ለሚከበረው የምዕተ ዓመቱ የኢትዮጵያ በዓልም ዝግጅት እንዲጀምር የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በዓል አከባበር ምክር ቤት ጠየቀ።
የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም በረደድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ህዝቡ ወጉን፣ልማዱን፣ባህሉንና ቅርሱን እንዲሁም ምርቱንና መልካም ገጽታውን ለዓለም ለማስተዋወቅ ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት።
ከብሄራዊ ምክር ቤቱ አላማዎች መካከል እያንዳንዱ ዜጋ በ2000 ዓ.ም ሁለት ችግኞችን እንዲተክል ማድረግ እንደሚገኝበትና በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በእያንዳንዳቸው ሁለት ሺ ዛፎችን በመትከል አንድ የሚሊኒዮም ፓርክ ለማቋቋም መታሰቡን አቶ ስዩም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ 2000ን በሙሉ በሚከበረው በዓል ህዝቡ የባህል ልብሶችን፣ቋንቋዎችንና ዳንሱን ፣ታሪኩንና ቅርሶቹን ከማስተዋወቅ ባሻገር የጋራ አገራዊ ራዕይና አመለካከት ለመፍጠርና ገቢውን ለማሳደግ በሚያመቸው አደረጃጀት ዝግጅቱን እንዲጀምር ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ምዕተ ዓመት በአል በሚከበርበት ዓመት የሀረር ከተማ አንደ ሺ ዓመት በዓል እንደሚከበር ተናግረው፤በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበብ ትምህርት ክፍልም 50ኛ ዓመት የልደት በዓሉን የሚያከብርበት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ 2000 ሚሊኒየም በዓል ብቸኛ የጥቁር ህዝብ በዓል በመሆኑ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም ተካፋይ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ ጨምረው አስረድተዋል።
ለበዓሉ አከባበር መንግስት የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በመሆኑ የተሟላ ፅህፈት ቤት አደራጅቶ ስራ የጀመረው ምክት ቤት የራሱን ድረ ገፅ በቅርቡ ይፋ በማድረግ በዓለምአቀፍ ደረጃ ስራውን እንደሚያፋጥን አቶ ስዩም አስታውቀዋል።
ለሚሊኒየም በዓል አከባበሩ ሁሉም ወገኖች አገራዊ ራዕይና በመፍጠር የጋራ ጥረት እንዲጀምሩና የመገናኛ ብዙሃንም ለምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
